Details
-
- ሰላም፡ ለዕድልህ፡ የተአምር፡ ዐምድ፨
- ገና፡ ሳትወልድ፡ ለወለደች፡ ዘውድ፨
- ዛሬማ፡ ጎልምሳ፡ ሲጠርሯት፡ በወንድ፨
- ምንም፡ አይደነቅ፡ ኤርትራን፡ ብትወልድ፨
- ቀድሞም፡ ተፀንሳለች፡ ባባ፡ ጠቅል፡ ሆድ፨
-
- ሰላም፡ እንላለን፡ ለዘውድህ፡ ቀጸላ፨
- የሕዝብህ፡ ሞገስ፡ ነው፡ የመንግሥትህ፡ ጥላ፨
- መነን፡ የዕድልሽ፡ ሚዛኑ፡ ሲሞላ፨
- መጣች፡ የባዕድ፡ አልጋ፡ ቈረቈረኝ፡ ብላ፨
- ኤርትራ፡ ልትኖር፡ ባባ፡ ጠቅል፡ ናላ፨
-
- ሰላም፡ ሰላም፡ ብልን፡ ምስጋና፡ እንቀጥል፨
- ስምህ፡ ቀዳማዊ፡ የሥላሴ፡ ኀይል፨
- በኤርትራ፡ ደግመህ፡ የኦሜድላን፡ ገድል፨
- ወልዳምላክነትህ፡ ታወቀ፡ ጠቅል፨
- የተለያየውን፡ አካል፡ ስትቀጥል፨
-
- ሰላም፡ እንላለን፡ ለራስህ፡ ጠጉር፨
- ተቀብቶ፡ ለቀባን፡ የነፃነት፡ ክብር፨
- ቀድሞም፡ ተፈሪ፡ ነው፡ የጠቅል፡ ታምር፨
- ዛሬማ፡ አርእስቱ፡ ሆኖ፡ ቀይ፡ ባሕር፨
- እዘልቃለሁ፡ ብሎ፡ ማንም፡ አይሞክር፨
-
- ሰላም፡ ለመልክህ፡ ላይናችን፡ (ብርሃን፡) ፋሲካ፨
- ሳይበሉ፡ እሚያጠግብ፡ ሳይጠጡ፡ እሚያረካ፨
- ፀሓያችን፡ ጠቅል፡ የኑሮአችን፡ ዋካ፨
- ይኑርልን፡ ዕድሜህ፡ ጥበብ፡ እያፈካ፨
- ኤልያስ፡ ባቆመው፡ የሕይወት፡ ፋብሪካ፨
-
- ሰላም፡ ለመምጣህ፡ ካሥመራ፡ መቀሌ፨
- ተቀበለህ፡ ሕዝቡ፡ እያለ፡ ሆበሌ፨
- ተማሮች፡ በመዝሙር፡ ካህናት፡ በሃሌ፨
- ሥዩም፡ የመላኩ፡ ሚካኤል፡ ምሳሌ፨
- ታማኝ፡ ነው፡ አስደሳች፡ ላባ፡ ጠቅል፡ ኀይሌ፨
-
- እምሥራቀ፡ ፀሓይ፡ እስከነዓረብ፨
- ተመስግኗል፡ ጠቅል፡ በዕውቀት፡ በጥበብ፨
- የትንሣኤ፡ መሪ፡ ሆኖ፡ ላለም፡ ሕዝብ፨
- ምንኛ፡ ይደንቃት፡ ይገርማት፡ ጄኔብ፨
- ጠላቶቹ፡ ረግፈው፡ ተፈሪ፡ ሲያብብ፨
-
- ከሁሉ፡ የሚሻል፡ ማመን፡ ነው፡ ግርማህን፨
- ጠቅል፡ ላትጎዳ፡ ከመጕዳት፡ ራስን፨
- ቤተ፡ ሰብም፡ ሆነ፡ ባዕዱም፡ ቢባንን፨
- ቃዥቶ፡ ለመቅረት፡ ነው፡ ጥሎ፡ የብብትን፨
- ዘበኛህ፡ አምላክ፡ ነው፡ ለጠቅል፡ እንደሆን፨